ለተቀናጀ የዓባይ ተፋሰስ ልማት የዩኒቨርቲዎች ሚና - display page
Asset Publisher
"አንድ ዕቅድ አንድ ሪፖርት፤ ለተቀናጀ የአባይ ተፋሰስ ልማት፤ በተፋሰሱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሚና" አስመልክቶ የምክክር መድረክ ነሐሴ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ተካሄደ፡፡ የውይይት መድረኩ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ከሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን አስራ ሁለት ዩኒቨርሲቲዎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል።
የውይይት መድረኩ ዋና ዓላማ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላና የግድቡ የአገልግሎት ዕድሜ እንዲረዝም ለማድረግ የተቀናጀ የዓባይ ተፋሰስ ልማት ለማከናወን ያለመ ነው፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ከሰላሌ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ ቅንጅታዊ አሰራርን እንዲፈጠር፤ በሁሉም የተፋሰስ ልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥና የተፋሰስ ልማት በተቀናጀ መልኩ ማከናወን መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
በመድረኩ ላይ የጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ወንዞችን በመገደብ የተፈጥሮ ሀብትን የመጠቀም መብት የተረጋገጠበት ነው ብለዋል። በግንባታው ሂደት ያጋጠሙ በርካታ እንቅፋቶች በመንግስትና ህዝብ ጥምረትና ቁርጠኝነት፣ የይቻላል መንፈስና ጥንካሬ ማለፍ ተችሏል ሲሉ አክለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከደለል በመከላከል እድሜው እንዲረዝምና ደህንነቱ እንዲጠበቅ የተፋስሰ ልማትና አፈር ጥበቃ ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልፀዋል። በዚህም በተፋሰሱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በጥናትና ምርምር ከሚጫወቱት ሚና ጎን ለጎን የተፋሰስ ልማትና አፈር ጥበቃ ተግባርን በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡