“በህብረት ቸለናል” በሚል መሪ ሃሳብ የፓናል ውይይት ተካሄደ - display page
Asset Publisher
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ነሃሴ 30/2017 ዓ.ም
“በህብረት ቸለናል” በሚል መሪ ሃሳብ ሚኒስትሮች፣ የፓርላማ አባላት፣ የጽ/ቤቱ አመራሮች፣ ምሁራን፣ የባለድርሻ አካላት፣ የዲያስፖራ አባላት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ ድርጅቶችና ግለሰቦችን ያሳተፈ የፓናል ውይይት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መ/ቤት አዳራሽ ተካሂዷል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ባዘጋጀው በዚሁ የፓናል ውይይት በታላቁ ህዳሴ ግድብ የ14 ዓመታት የመንግስትና የህዝብ ትግልና ሁለንተናዊ ተሳትፎ፣ የግድቡ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች፣ ግድቡ ለቀጠናዊና ለአፍሪካ አህጉር ያለው አስተዋጽኦና ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከቱ ርዕሰ ጉዳዮች ቀርበዋል፡፡
የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የጽ/በቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ክቡር አረጋዊ በርሄ (ፒኤችዲ) ለግድቡ ምረቃ ስለበቃን እንኳን ደስ ያላችሁ፤ በኛው ላብ፣ ደም፣ ዕውቀት፣ ገንዘብ፣ ትብብርና አንድነት ይህንን ታላቅ ፕሮጀክት ለፍሬ አብቅተናል፤ የነጋችንም ተስፋ አለምልመናል ብለዋል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ደዒታ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ የፓናል ውይይቱን ሲያስጀምሩ እንደገለጹት ያለ ውጪ ሀገራት ብድር በራስ አቅም ሃገራችን ሳትጠበቅ ትልቁን ገድል ፈጽማለች፤ ይህንን ዕውን እንድናደርግ ትልቅ አቅም የሆነንን የአንድነትና የመተባበር እሴት በሌሎች ሃገራዊ የልማት ስራዎችም ላይ ማስቀጠል አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የፓናል ውይይቱን ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድር ኮሚቴ ሰብሳቢ የመሩት ሲሆን አቶ ዛዲግ አብርሃ የአፍሪካ ልህቀት አካዳሚ ዋና ስራ አስፈጻሚ፣ አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ የውሃ ሀብት አስተዳደር፣ ድንበር ተሻጋሪና የውሃ ዲፖሎማሲ ምሁር እና አቶ ጌታቸው ግዛው በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሄራዊ አረንጓዴ አሻራ ቴክኒክ ኮሚቴ ም/ል ሰብሳቢ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡ ከፓናሊስቶቹ ማብራሪያዎች በኋላ በተካሄደው የውይይት ጊዜ በመድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎች የተለያዩ ሃሳቦችና ጥያቄዎችን አንስተው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በመዝጊያ ንግግራቸው በህዳሴ ግድብ አንድ ዕርምጃ ወደ ፊት ተራምደናል፤ ከፊታችን ብዙ ዕርምጃዎች ይቀሩናል፤ ሌሎች ግድቦች ሌሎች የልማት ስራዎች ይጠብቁናል፤ ይህ የሁሉም ትኩረትና ጉዳይ መሆን አለበት ብለዋል፡፡