Asset Publisher

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ተመረቀ

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ጳጉሜ 04/2017 ዓ.ም የተለያዩ ሃገራት መሪዎችና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የፌደራል፣ የክልልና የከተማ መስተዳድር ባለስልጣናት፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ የሀገሪቱ ከፍተኛ የጦር አዛዦች፣ በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በተገኙበት በድምቀት ተመርቋል፡፡

 

 

 

የዓለም ትኩረትን በሳበው የምረቃ ዝግጅት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በክብር ዕንግድነት የተገኙት የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ (ዶ/ር)፣ የጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦመር ጊሌህ፣ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ (ዶ/ር)፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት፣ የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ አሞር ሞትሊ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የእስዋቲኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሴል ሚሶ ድላሚኒ፣ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ፣ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ክላቨር ጋቴቴ በክብር ዕንግድነት ታድመዋል፡፡

ዶ/ር ዐብይ በንግግራቸው ለግድቡ መጠናቀቅ ከፍተኛ ድጋፍ ላደረጉ ድርጅቶች፣ ተቋማት፣ ግለሰቦች፣ ለመላ ኢትዮጵያውያንና የትዮጵያ ወዳጆች ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ለዚህ ታላቅ ገድል ስለበቃን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ “ታሪክ ሰምተናል፣ ታሪክ አይተናል፣ ታሪክ ተምረናል፡፡ በእግዚአብሄር ፈቃድ ግን እኛ የዛሬው ትውልድ ታሪክ ሰርተንና ታሪክ ላይ ቆመን ለመናገር በቅተናል፡፡ ህዳሴ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ህዝቦች በሙሉ ምድር እስክትሰበሰብ ድረስ ታሪክ ሆኖ የሚኖር ታላቅ ገድል ነው፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ለግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችም የክብር ኒሻን አበርክተዋል፡፡

 

ሌሎች ንግግር ያደረጉ መሪዎችም የታላቁ ህዳሴ ግድብ በቀጠናው ብሎም ለመላው አፍሪካ የሀይል አቅርቦትን በማሳደግ ፣ የሀገራት እርስ በርስ ግንኙነቶችን በማጠናከር፣ የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤን በማጉላትና በሌሎችም ጉዳዮች የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑንና ሌሎችንም የሚያነሳሳ በፕሮጀክት አፈጻጸምም ምሳሌ የሚሆን ትልቅ ታሪክ እንደተከናወነ አመላክተዋል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ላለፉት 14 ዓመታት ለግድቡ ግንባታ ህብረተሰቡ በተለያየ መልኩ ሲያደርጋቸው የነበሩ ሁለንተናዊ ድጋፎችን በማስተባበር ሃብት በማሰባሰብ እና የሞራል፣ የሙያና የአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ተሳትፎዎችን በመምራት የማይተካ ኃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡ በገንዘብ ድጋፍ ብቻ በአጠቃላይ ከ24.5 ቢሊ ብር በላይ በቦንድ ግዥ፣ በስጦታና በተለያየ መልኩ ከህብረተሰቡ ማሰባሰብ የተቻለ ሲሆን ይህም ለግድቡ ግንባታ ከዋለው ወጪ ከ10.3 % በላይ የሚሆን ነው፡፡