Publicador de contenidos

በህዳሴ ግድብ ተፋሰስ ችግኝ ተከላ

በህዳሴ ግድብ ተፋሰስ ችግኝ ተከላ ተካሄደ
ሐምሌ 24 ቀን 2018 ዓ.ም (ታላቁ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት) በኦሮሚያ የታ/ሕ/ግ/ማስ/ጽ/ቤት አስተባባሪነት በህዳሴ ግድብ ተፋሰስ ችግኝ ተከላ ተካሄደ፡፡ "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሀሳብ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ የተከናወነው በምዕራብ ሸዋ ዞን ቶኬ ኩታዬ ወረዳ በአባይ ጉደር ተፋሰስ ላይ ነው፡፡
በችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የታላቁ ህዳሴ ግድብ የማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ፍቅርተ ታምር ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሀገራችን እየተካሄደ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡ ሀገራችን የተፈጥሮ ሀብቷን፣ ለም አፈሯን፣ ውሃዋንና የአካባቢ ስነምህዳርን ወ.ዘ.ተ. የመንከባከብና የመጠበቅ ተግባራትን እየሰራች እንደምትገኝም ተናግረዋል፡፡ በያዝነው በጀት ዓመትም በአገር አቀፍ ደረጃ ከስምንት ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል የተያዘውን ግብ መሰረት በማድረግ የሚከናወነው ይህ መርሃ-ግብር፤ አረንጓዴ አሻራን በማሳረፍና ሀገራዊ ሀላፊነትን ለመወጣት ያለመ እንደሆነ ተናግረዋል። በዚሁ መሰረት በአባይ ጉደር ተፋሰስ ላይ የሚከናወነው ደግሞ በተለየ መልኩ የህዳሴ ግድብን ከደለል ለመጠበቅና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን ለመስራት ሚና ያለው ሲሆን ተጨማሪ ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ የታ/ሕ/ግ/ማስ/ፕ/ጽ/ቤት ዋ/ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ቆንጅት በቀለ የግችኝ ተከላው መርሃ-ግብር ዋና ግቡ የአካባቢ ጥበቃና የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለሀገራዊ መግባባት፣ ለአብሮነትና ለማህበራዊ መስተጋብር መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል። በየዓመቱ በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ የአባይ ተፋሰስ አካባቢዎች የችግኝ ተከላው ተጠናክሮ እየተካሄደ መሆኑን የገለፁ ሲሆን ይህም ግድቡን ከደለል ለመከላከልና የአገልግሎት ዘመኑን ለማራዘም የራሱ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡
አረንጓዴ አሻራ የአገራችንን የከባቢ አየር ደህንነት ለመጠበቅ፣ የደን ሽፋንን ለማሳደግ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና ለቀጣይ ትውልድ አረንጓዴ ከተማ ለማስረከብ የሚካሄድ ሀገራዊ እንቅስቃሴ ነው። ችግኝ መትከል አካባቢን ከማስዋብ በላይ የነገን ህይወት መጠበቅ ነው። ስለሆነም በችግኝ ተከላው መርሃ-ግብር በንቃት በመሳተፍና በቀጣይም በመንከባከብ ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውሉ ለማድረግ አረንጓዴ፣ ውብ እና ለኑሮ ምቹ አካባቢ መፍጠር የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ኃላፊነት ነው።